በእለቱ አብነት አጎናፍርን ጨምሮ የሁለት አርቲስቶች የአልበም ምርቃት፣ የክብር ስጦና እና የፊርማ ስነ ስርአትም ተከናውኗል።
ሀገር በቀሉ የሙዚቃ አገልግሎት ሰጪው “ሰወሰው” መተግበሪያ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
የስምምነት ፊርማው በሰዋሰው መተግበሪያ እና በሰዋሰው ዩትዩብ ቻናል በኩል የሚሰራጩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን የቅጂ መብት ለማስከበር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል ።
ይህ ስምምነት የኪነ-ጥበብ ስራዎቹ ተደራሽነት ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የመዝናኛውን ኢንዱስትሪ ዲጅታላይዝ በማድረግ በኩል አሻራውን በማሳረፍ ላይ የሚገኘው ሰዋሰው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በገባው ስምምነት ከነበሩት የክፍያ አማራጮች በተጨማሪ ወደ 9107 አጭር ቁጥር A ወይም B ብሎ በመላክ እለታዊ እና ሳምንታዊ የክፍያ የደንበኝነት ጥቅሎችን በመግዛት ደንበኞች የሚፈልጉትን ሙዚቃ እንዲያገኙ ያስችላል።
ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ የሚሰሩት ሐበሻ ቪው እና ቴሌጌም ይፋ በተደረገው ስነ-ስርአት ላይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን ፊርማ አኑረዋል።
የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ ለማዘመን እና ለማሳደግ እየተጋ የሚገኘው ሰዋሰው በአዲስ አበባ ኃይሌ ግራንድ ሆቴል በተካሄደ ስነ-ስርአት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በተፈራረመበት ወቅት 2 የሙዚቃ አልበሞች እና 1 የሙዚቃ ቪድዮ በመተግበሪያው እና በዩትዩብ ቻናሉ አሰራጭቷል።
የሙዚቃ አልበሞቹ የአብነት አጎናፍር “አለቀ” እና የታምራት ካህሳይ “ዋካይ” የተሰኘው የትግርኛ አልበም ናቸው።
በኤርሚያስ ማላ የተሰራው “ህልሜ” የተሰኘ ሙዚቃ ቪድዮ ደግሞ በሰዋሰው ዩትዩብ ቻናል በኩል ለሙዚቃ አድማጮች ተሰራጭተዋል።
በተጨማሪም ድምጻዊ ታደለ ሮባ እና ብርሃኑ ዘተራ (ላፎንቴን) እና ድምጻዊት ጸደንያ ገ/ማርቆስም ከሰዋሰው ጋር ተፈራርመዋል።
የተመረጡ ኦርጅናል የሙዚቃ ስራዎችን ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ለሙዚቃ አፍቃሪያን በማቅረብ ላይ የሚገኘው “ሰዋሰው” መተግበሪያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል ስራዎቻቸውን ለሕዝብ ካደረሱ ድምጻዊያን መካከል አስቴር አወቀ፣ ማሪቱ ለገሰ፣ ግርማ ተፈራ እና ካሙዙ ካሳ ይገኙበታል።