መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር እየተደረገ ስላለው ድርድር መረጃ እንዲሰጥ ተጠየቀ

መንግሥት ‹‹ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት›› ጋር ስለሚያደርገው ድርድር በቂ መረጃ ይስጥ ሲል ኢዜማ አሳስቧል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መንግሥት ራሱን ‹‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት›› ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር ስለሚያደርገው ድርድር በቂ መረጃ ይስጥ ሲል ጠይቋል፡፡ 

ፓርቲው በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ሲገደሉ ንብረታቸውም ሲወድምና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በግልጽ ተመልክተናል ብሏል፡፡

መንግስትም በተደጋጋሚ የተፈፀሙትን በደሎች ይህ ታጣቂ ቡድን ሲፈፅማቸው እንደነበር ከማሳወቁ አንፃር ይህን መሰል የዜጎች ሰቆቃ የሚያስቆም ድርድር ውስጥ መግባቱን ፓርቲው እንደሚደግፈው ገልጿል፡፡ 

ይሁንና ብልጽግና ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረበትን ጊዜ ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የሚፈጸሙ ድርድሮች ግልጽነት የጎድላቸው እና አፈፃፀማቸው ደካማ መሆናቸውን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ለአብነትም ከሕወሓት ጋር ድርድር ቢደረግም በስምምነቱ መሰረት ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን አስተውለናል ያለው ፓርቲው ቀጣይ ሂደቶችም ምን እንደሚሆኑ አይታወቅም ብሏል፡፡

በመሆኑም መንግስት ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኦነግ ከኤርትራ ወደ ሀገር ቤት ከገባ በኋላ በስምምነቱ መሠረት አልተፈጸመልኝም ሲል አንደነበረው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ሲል አሳስቧል፡፡

አሁን ላይ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር እየተደረጉ ያሉ ድርድሮችን በሚመለከት እነማን እየተሳተፉ እንደሆነ፣ የስምምነቱን ይዘት፣ እንዴት እንደሚፈጸም እና በአፈፃፀሙም ጊዜ ተግባራዊነቱን ለዜጎች ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት እና ‹‹በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት›› መካከል በታንዛንያ ድርድር መጀመሩ ከተነገረ አንድ ሳምንት ቢሞላም፤ እስካሁን ድረስ ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *