ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝም ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ ምላሽ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ ምክር ቤቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዮች እውቅና መስጠቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝና የምክር ቤቱ መግለጫም ይሄንኑ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመልክቷል።
ሕብረቱ በዘላቂ ግብርናና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረውን ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ ፕሮግራም በድጋሚ ለመጀመር ያሳየውን ዝግጁነት፣ አበዳሪ አገራት ባቋቋሙት የጋራ ማዕቀፍ ስር የሚከናወነው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የድርድር ሂደት በአፋጣኝ እንዲቋጭ ያቀረበው ጥሪና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማረጋጊያና ማሻሻያ አጀንዳ እንዲደግፉ የሰጠው ጠንካራ ማበረታቻ መልካም የሚባል እንደሆነ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች ወዳጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የማስቀመጫው ጊዜ አሁን ነው ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።
ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ከህወሀት ጋር ባሳለፍነው ህዳር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከምዕራባዊያን ሀገራት ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ ይገኛል።
በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የኢኮኖሚ እና እርዳታ ማዕቀቦችም እየተለቀቁ ሲሆን በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ዳግም እንዲያገግሙ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።