አንድ የአሜሪካ ዜጋ ሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ውጊያ መገደሉ ተሰምቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፎክስ ኒውስ በሰጠው ቃል ፤ በሱዳን አንድ አሜሪካዊ ዜጋ መሞቱን አረጋግጧል።
መስሪያ ቤቱ ፤ ከሟች ቤተሰብ ጋር እየተገናኘ መሆኑንና በደረሰባቸው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
“በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለቤተሰብ ካለን አክብሮት የተነሳ ምንም የምንጨምረው ነገር የለም ” ሲልም ስለ ሟች ዝርዝር መረጃ ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
በሌላ በኩል ፤ የአሜሪካ መከላከያ ጦር በአፍሪካ ኮማንድ በኩል በሱዳን ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ መሆኑን አሳውቋል።
አሜሪካ በሱዳን ያሉ ዜጎቿን ደህንነት ለማረጋገጥ ወደ ጅቡቲ ተጨማሪ ወታደሮችን ለመላክ እያሰበች መሆኗንም አስታውቃለች።
የአሜሪካ ጦር ፤ በካርቱም የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞችን እና ዜጎችን ለማስወጣት የሚያስችለውን ተልዕኮ ለመፈፀም ተጨማሪ ኃይሎቹን ጅቡቲ ለማስቀመጥ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተሰምቷል።