በኢትዮጵያ ተጨማሪ አምስት ቴሌቪዥኖች ወደ ስርጭት ሊገቡ ነው ተባለ

አምስት የንግድ የቴሊቪዥን ጣቢያዎች የስርጭት ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አምስት የንግድ የሳተላይት ቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎት ጣቢያዎች ፈቃድ እንዲሰጣቸው  መወሰኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን አስታውቋል።

ፈቃዱን የሚያገኙት ጎህ ቴሌቪዥን፣ ኤፕላስ ቲቪ፣ ሸካል ቲቪ፣ ከገበሬው ቴሌቪዥን እና ኢሲኤን ቴሌቪዥን መሆናቸውን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ፈቃድ የሚሰጣቸውም የገንዘብ አቅምና ምንጫቸው ስራውን ለማስኬድ አስተማማኝ እንደሆነ በመታመኑ ነው ያለው ባለስልጣኑ፣ አገልግሎቱን ለመስጠት ድርጅታዊ ብቃት ያላቸው መሆኑ መጣራቱ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የፕሮጀክት ሰነዳቸው፣ ያቀረቧቸው መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች አገልግሎቱን ለመስጠት ብቃት ያላቸው መሆናቸው ተጣርቶ መወሰኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡


የንግድ ቴሌቪዥን ፈቃድ ለማገኘት የቀረቡ አመልካቾች በባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት በመቅረብ ውል እንዲዋዋሉና ከዛሬ ጅምሮ ፈቃዳቸውን መውሰድ እንደሚችሉም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ 27 የግል እና 17 የመንግስት ቴሌቪዥን ማሰራጫዎች ሲኖሩ የማህበረሰብ ሬድዮኖችን ጨምሮ በድምሩ 70 የሬድዮ ጣቢያዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን መረጃ ያስረዳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *