ኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞችን ወደ ሳውዲ አረቢያ መላክ ጀመረች

Ethiopian housemaids

ኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመላክ በምልመላ ላይ እንደሆነች ተገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የሴቶች የጅምላ ምልመላ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል ።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የሳውዲ አረቢያ የሰብዓዊ መብት አያያዟ ደካማ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የሴት ሠራተኞች የጅምላ ምልመላ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

አሁንም ቢሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች በሳውዲ አረቢያ ከሠራተኛ ሕጎች የተገለሉ እና በዘመናዊ ባርነት ስርዓት ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው ተብሏል፡፡

“ካፋላ” በተሰኘው ስርዓት አንድ ሠራተኛ በደል ቢደርስባት እና ከአሠሪዎቿ ብትሸሽ ፓስፖርቷን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ መረጃዎቿን እንድታጣ እንደሚደረግ እና ይህ ስርዓት አሁንም ለውጥ እንዳልተደረገበት ተገልጿል።

‹‹ሳውዲ አረቢያ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ በማሰር እና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ለእንግልትና ለሞት በመዳረግ፤ ሌሎችንም በመደብደብ ከአገሯ እንዲወጡ አድርጋለች›› ሲሉ የስደተኞች መብት ተመራማሪ ናድያ ሃርድማን አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ ይህን ዓይነት አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ወዳለባት ሳውዲ አረቢያ 500 ሺሕ ሴት ሠራተኞችን ለመላክ ማቀዷን የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎቹ ኮንነዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሚላኩት ሴት ሠራተኞች ከሳውዲ አረቢያ የሠራተኛ ጥበቃ ሕጎች የተገለሉ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ለሚደርስባቸው በደልም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መፍትሔ የሌላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞችን ለተሳዳቢ አሠሪዎች አሳልፎ የሚሰጠውን የካፋላ ስርዓትን ማፍረስን ጨምሮ ሙሉ ጥበቃን ለማረጋገጥ መፍትሔ መፈለግ አለበትም ተብሏል።

 የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፣ በውሸት የጥበቃና ዋስትና ከለላ ሴቶችን ወደ ስደት መገፋፋት የለበትም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዘንድሮው በጀት ዓመት የ500 ሺሕ ሴቶችን የጉዞ ወጪ ችሎ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመላክ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

የመጀምሪያ ተጓዦች ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ወደ ሪያድ ተጉዘዋል፡፡

በ266 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ለቤት ሠራተኝነት የሚሄዱት የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ከ18 እስከ 40 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ የኮሌጅና የዩንቨርሲቲ ምሩቃንንም ያካተተ ነው፡፡

ሠልጣኞች ከመንግሥት በኩል እድሉ ሊያመልጣቸው የማይገባ የሕይወት ዘመን ወርቃማ እድል ነው መባላቸውን ገልጸዋል፡፡

በፈርንጆች 2020 የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስቃይና መገደል ካረጋገጠ በኋላ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያወግዝ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት የነበሩ 100 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *