የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ እንዳለው በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 200 ከፍ ማለቱን ገልጿል።
ኮሚቴው እንዳለውም የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 1500 በላይ መድረሱንም ጠቅሷል።
ነገር ግን በተመድ ሪፖርት መሰረት የሟቾች ቁጥር 185 መሆኑን አስታውቋል።
በሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ(አርኤስኤፍ) መካከል ባለፈው ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ጦርነት አራተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ሀገራት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ተመድ በበኩሉ አሁን ላይ በሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ድርድር ለመጀመር ፍቃደኝነት የለም ብሏል።
በሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በሀይል በ2019 ከተነሱ በኋላ የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከስቷል።
ስልጣን የተቆጣጠረው የሱዳን ወታደራዊ አስተዳድር በሲቪል የሚመራ መንግሥት እንዲመሰረት ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ሲጠይቅ ቆይቷል።
ይሁንና የሱዳን ወታደሮች ለሁለት ተከፍለው ስልጣን በሀይል ለመቆጣጠር ወደ ጦርነት ገብተዋል።