ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው ፍርድ ቤት ቀረቡ

ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በማለት ተጠርጥረው ከአራት ቀናት በፊት ታስረው የነበሩት ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ ሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው።

ፖሊስ ተጠርጣሪ ጋዜጠኞቹን ፍርድ ቤት አቅርቦ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው፣ ጋዜጠኛ ዳዊት አራት ኪሎ ሚዲያ፣ የሚባል የኦንላይን ሚዲያ ፈቃድ ሳይኖረው በመክፈት ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና አንዱን ሐይማኖት ከሌላው ጋር ለማጋጨት በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ እንደደረሰበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስም ኢትዮ ሰላም የሚባል የኦንላይን ሚዲያ ፈቃድ ሳይኖረው በመክፈት ሲሰራ እንደነበርና ሁለቱንም ተጠርጣሪዎች እየመረመረ መሆኑን አስረድቶ ለተጨማሪ ምርመራ 14ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ፈቃድ ለማውጣት የሚገደዱበት የሕግ መሠረት እንደሌለ በማስረዳት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ተከራካሪዎች አዳምጦ፣ ፖሊስ ከጠየቀው ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለሚያዚያ 16 ቀን 2015 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በቁጥጥር ስር የዋለው በባሕርዳር ከተማ ሲሆን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ደግሞ በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑ ይታወቃል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *