የኢትዮጵያ ብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ማህበር በጋዜጠኞች እስር ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
ማህበሩ እንዳለው ብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ስህተት በሚሰሩበት ወቅት ደግሞ በህግ አግባብ መጠየቅ እንዳለባቸው እና የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበት እንደሚያምን ገልጿል።
ይሁንን ” ከለውጡ በኋላ ” በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዲረጋገጥ ማህበራችን ብዙ ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ባለሙያዎች የሚሰሩበት አውድ እየጠበበ ጋዜጠኞች ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ በመንግስት የፀጥታ አካላት እየተሸማቀቁ እና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ማህበሩ በመግለጫው ላይ ጠቁሟል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር መስራችና የስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ አራጋው ሲሳይ ፣ ገነት አስማማው ፣ ጌትነት አሻግሬ ፣ በየነ ወልዴና ቴዎድሮስ አስፋው በመንግስት ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋልም ብሏል።
ከታሰሩት ጋዜጠኞች ውስጥ የተወሰኑት ያሉበት ቦታ እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንኳን ቤተሰቦቻቸውም በቂ መረጃ የላቸውም ተብሏል።
ጋዜጠኞች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ እየታሰሩ፣ እየታፈኑና ቤታቸውና ቢሯቸው እየተበረበረ መሆኑ ባለሞያዎች ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ፤ የፕረስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ ማድረጉንም ማህበሩ ገልጿል።
ማህበራችንም የተቋቋመው እንደዚህ አይነት ሙያውን የሚያቀጭጩ ጫናዎችን ለመታገል በመሆኑ እርምጃዎችን በፅኑ አወግዛለሁም ብሏል።
ጋዜጠኞች በወንጀል ሲጠረጠሩ ጉዳያቸውን እስር ቤት ሳይቆዩ መከታተል እንደሚችሉ ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቢደነገግም ተግባራዊ አለመደረጉ ማህበሩን እንዳሳበበውም አስታውቋል።
መንግስት የፕረስ ነፃነት እንዲረጋገጥ ያጸደቃቸውን ህገ-መንግስታዊና ዓለም አቀፋዊ ህጎች እንዲያከብርና ውስጡን እንዲፈትሽ እንዲሁም ያለምንም የህግ አግባብ ያሰራቸውን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲፈታ እና ባለሙያዎች ላይ የሚያደርሰውን ማሸማቀቅ እንዲያቆም ማህበራችን ጠይቋል።
በዚህ አጋጣሚ ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎች ማህበራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የማህበራችን አጋር በመሆን በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዲረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥበቃ ተቋም ወይም ሲፒጂ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን እያሰረች መሆኑን እና የታሰሩ ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ መጠየቁ ይታወቃል።