በደብረ ብርሃን ውሃ ተበክሏል እየተባለ የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑ ተገለጸ

የደብረብርሃን ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት መሰረት መንገሻ እንደገለጹት ከትላንት ጀምሮ መርዝ ተጨምሮበት ውሃ ተበክሏል እየተባለ የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ተቋማቸው አንዱ ተግባሩ የሚያመርተውን ውሃ ጥራት አረጋግጦ ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት ሃላፊነታቸው በመሆኑን ባለሙያዎች እሁድ ቅዳሜን እና የበዓላትን ቀናት ጭምር አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ታጥረው የሚጠበቁ ከመሆኑም በላይ ሁል ጊዜ በባለሙያ ክትትል እየተደረገላቸው ውሃው በባለሙያ ጥራቱ ተረጋግጦ ለደንበኞች እንደሚሰራጭ አረጋግጠዋል፡፡

የፀጥታ ችግር ሲከሰት ደግሞ በልዩ ሁኔታ ጥበቃና ክትትል እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡

ችግር ካጋጠመም ውሃው እንደማይለቀቅ ጠቅሰው ህብረተሰቡ የውሃ ተቋሙ የሚያደርገውን ጥንቃቄ በአግባቡ ተረድቶ በአሉባልታ ወሬ እንዳይረበሽ መክረዋል፡ ውሃው 100 ፐርሰንት ንጹህ መሆኑን ስራ አስኪያጇ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በከተማው የውሃ እጥረት ችግር መኖሩን ጠቅሰው ሰሞኑን ደግሞ በመብራት ችግር ሶስት የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት ባለመስጠታቸው እጥረቱ መባባሱን አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመቀነስ በጀነሬተር እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቁመው በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በከተማው ውስጥ በመኖራቸው ጫናው ከፍ ያለ መሆኑን ስራ አስኪያጇ ገልፀዋል፡፡

ጫናው ሰፊ ቢሆንም የተቋሙ ሰራተኞች ሁልጊዜ በስራ ላይ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በማንኛውም ሰዓት መዘጋት ስለማይችልም ስራውን በትጋት ያከናውናል ማለታቸዉን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *