ግዙፉ የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፋብሪካ መገንባት እንደሚፈልግ ገለጸ

በቻይና በሲሚንቶ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ ሲኖማ ዓለም አቀፍ ኩባንያ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፋብሪካ መገንባት እንደሚፈልግ ገልጿል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው የሲኖማ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሊቀመንበር እና የሲኤንቢኤም ተቋም ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ሚስተር ሉ ያን እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተወያይተዋል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚደረግበት ዙሪያ ቤጂንግ በሚገኘው የኩባንያው ዋና ጽ/ቤት ተገኝተው ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ተፈራ በውይይቱ ወቅት ኩባንያው በኢትዮጵያ ባሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከዲዛይን ጀምሮ በግንባታ ረገድ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በኢትዮጵያ ካለው የግንባታ ስፋት አንጻር የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

አምባሳደር ተፈራ አያይዘውም፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ቢሰማራ የጋራ ተጠቃሚነቱ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 26እስከ 28 ቀን 2023 በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኩባንያው ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚስተር ሉ ያን በበኩላቸው፣ ለአንድ አገር ዕድገት ሲሚንቶ እና ብረት ወሳኝ ግብዓቶች መሆናቸውን ጠቁመው፣ ዘመኑ ያፈራውን ምርጥ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖ የማይኖረው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመገንባት ሐሳቡ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኩባንያው ኃላፊ በኤምባሲው የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው በኢንቨስትመንት ፎረሙ የሚሳተፍ ቡድን የሚልኩ መሆኑን መግለጻቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *