ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸመት ቀዳሚ መሆኗ የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይ ባለፈው ጥር ወር ያስገባቸው የኃይል መጠን በታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
ይህ የሆነውም በምስራቅ አፍሪካ ባጋጠመው አስከፊ ድርቅ ምክንያት የኃይል ማመንጫ ግድቦች ውሃቸው በመድረቁ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከኬንያ ስታትስቲክስ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ አገሪቱ ባለፈው ጥር ወር 68 ነጥብ 48 ሚሊዮን ኪሎዋት ኤሌክትሪክ ኃይል አስገብታለች፡፡
ኹለቱ አገራት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል በቅናሽ ለመገበያየት ከተስማሙ በኋላ፤ ኬንያ 39 ሚሊዮን ዩኒት ኃይል ከኢትዮጵያ ማስገባቷ ተነግሯል፡፡
በዚህም አገሪቷ በርካሽ ዋጋ ኃይል ለማስገባት ከተስማማች በኋላ ጥር ላይ 200 ሜጋዋት የኤሌክትርክ ኃይል ከኢትዮጵያ ማስገባቷ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም የኃይል አቅርቦቱን ለማረጋጋት እንዳስቻላት ተጠቁሟል፡፡
ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ለ25 ዓመታት የሚቆይ የኤሌክትሪክ ኃይል የግዥ ስምምነት እንዳላት ተመላክቷል፡፡ በዚህም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ከህዳሴ ግድብ 200 ሜጋዋት የምትወስድ ሲሆን፤ በቀሪዎቹ ዓመታት ወደ 400 ሜጋዋት ከፍ እንደሚል ተጠቅሷል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ኬንያ የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሎች የኃይል አምራቾች በእጅጉ ባነሰ ዋጋ በአንድ ኪሎዋት 6 ነጥብ 5 የአሜሪካ ሳንቲም እየገዛች ነው ተብሏል፡፡
አስራ ስድስት የኃይል ማመንጫ ግድቦች ያላት ኬንያ በድርቅ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ምርቷ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተጠቁሟል፡፡
አገሪቱ የኃይል አቅርቦት ችግሯን ለማረጋጋት ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ከፍተኛ ኃይል የምታስገባው ከዩጋንዳ መሆኑም ተነግሯል፡፡