በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ህገ-መንግታዊ እውቅና እንዲሰጠው ተጠየቀ

ሩትስና ዊንግስ የተባለ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት የምልክት ቋንቋ በሚሊዮኖች ቢነገርም ተገቢውን እውቅና አላገኘም ብሏል።

ከተመሰረተ ሁለት ዓመት የሞላው ድርጅቱ ይህም በመሆኑ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በቋንቋቸው የመማር፣ የመገልገልና መረጃ የማግኘት መብታቸው እንደተገደበ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ እንደሌሎች ቋንቋዎች “ሀገርኛ” ቢሆንም እንዳላደገ ተነግሯል።

የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ሰርካለም ግርማ (ዶ/ር) ለአል ዐይን  የምልክት ቋንቋ በቋንቋ ፖሊሲው እንዲካተት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።ፖሊሲው ገና ባለመጽደቁ “ተስፈኞች” ነን ብለዋል።

ከ90 በመቶ በላይ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎች ቋንቋቸውን የሚማሩት ት/ቤት ቢሆንም ሀገሪቱ ካሏት ት/ቤቶች አንድ በመቶ የማይሞሉት ብቻ ‘አካቶ ትምህርት የሚያስተምሩ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት እያሱ ኃይሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ቋንቋው እንዲያድግና ትኩረት እንዲሰጠው የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ጥያቄ ሊቀርብም ነው ተብሏል።

ሩትስና ዊንግስ የምልክት ቋንቋ እውቅና እንዲያገኝ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በደብዳቤ ጥያቄ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በደብዳቤው በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች መስማት የተሳናቸው ናቸው ያለው ግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ “ቋንቋው ሰዋሰው ያሟላ፣ መዝገበ ቃላትና ዘዬ ያለው የተሟላ ቋንቋ ነው” ብሏል።

መስማት የተሳናቸው ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ፣ ለማህበረሰቡም እንዲቀርቡና በቋንቋቸው አገልግሎት እንዲያገኙ መደላድል ለመፍጠር የምልክት ቋንቋ እውቅና እንዲያገኝ ጥያቄው እንደሚቀርብ ተነግሯል።

መንግስት ይህን ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፍ ከቃል በላይ ያለውን ኃላፊነት እንዲወጣም ተጠይቋል።

ሩትስና ዊንግስ “እጆች ይናገራሉ፤ አይኖች ይሰማሉ” በሚል ግንዛቤ ለመፍጠርና የምልክት ቋንቋ እውቅና እንዲያገኝ ጫና ለመፍጠር ለአንድ ወር የሚቆይ ማህበራዊ ንቅናቄ አካሂዳለሁ ብሏል።

ድርጅቱ ለቋንቋው ማደግ አበርክቶ እንዲወጡ ለተቋማት፣ ምሁራን፣ ሚዲያዎችና የተለያዩ አካላትም ጥሪ አቅርቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *