በአማራ ክልል ልዩ ኃይልን እና በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጥረት መፈጠሩ ተገለጸ

የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ በመጀመሩ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፤ በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ፡፡

የክልሉን ልዩ ኃይል ያለ በቂ ዝግጅት፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን አብን አስታውቋል፡፡

ጉዳዩ በአማራ ክልል ብቻ ሳይወሰን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር፣ ክልሉን እና  ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ መሆኑን አብን ለፌዴራሉ መንግሥትና ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አሳስቧል፡፡

በመሆኑም፣ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እና ከአማራ ክልል መንግሥት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ አብን ጠይቋል፡፡

በካምፕ እና በግዳጅ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት በሙሉ የተፈጠረው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

ልዩ ኃይሉ በጥንቃቄ  እና መረጋጋት ራሱን እንዲጠብቅ እና የተፈጠረው ችግር በውይይት እና በመነጋገር እንዲፈታም አብን ጠይቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግስት እና ህወሃት መካከል ላለፉት ሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ መቆሙ ይታወሳል፡፡

የአማራ ልዩ ሀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ ህውሃትን ሲዋጋ የቆየ ሲሆን በተለይም የሀገር መከላከያውን ከከፋ ጉዳት ሲከላከል ቆይቷል፡፡

ይሁንና የፌደራል መንግስት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የክልል ልዩ ሀይሎች ተጥቃቸውን ይፍቱ የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

የአማራ ክልል በተለያ ከህወሃት እና ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የደህንነት ስጋት ያለበት ሲሆን ከሌሎቹ ቀድሜ ተጥቅ አልፈታም የሚል ተቃውሞ በማሰማት ላይ ነው፡፡

የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎች ተጥቅ ይፍቱ ይበል እንጂ የሌሎች ክልል ልዩ ሀይሎችን ተጥቅ ማስፈታት አልጀመረም፡፡  

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *