መልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ለአማርኛ እና ኦሮሚኛ ተመልካቾች አዳዲስ ፕሮግራሞችን እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ከመልቲቾይዝ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ዲኤስቲቪ ለኢትዮጵያ ተመልካቾች የተለያዩ መዝናኛ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ የይዘት ቀንን በአዲስ አበባ ያከበረ ሲሆን በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ብዙሃን መገኛኛ ባለሙያዎች እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

ድርጅቱ በዚህ ወቅት እንዳለው ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ሲያቀርባቸው ከነበሩት የመዝናኛ ፕሮግራሞች በተጨማሪ አዳዲስ ይዘቶችን እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡

በድርጅቱ በኩል ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ይቀርቡ ከነበሩት ይዘቶች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮግራሞችን በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሚተላለፉ ይዘቶችን በቅርቡ እጀምራለሁም ብሏል፡፡

ዲኤስቲቪ አሁን ላይ በአቦል ቲቪ እና አቦል ዱካ ፕሮግራሙ አደይ፣ ደራሽ፣ አስኳላ፣ ሶረኔ፣ አጋሮቹ፣ ገብርዬ እና ሌሎችንም መዝናኛዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

የመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገሊላ ገብረሚካኤል በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት ድርጅቱ በቀጣይ ለኢትዮጵያ ተመልካቾች ከእስካሁኖቹ በተጨማሪ እንደ አንድ፣ አፋፍ፣ ጊዜ፣ ቁጭት፣ ዳግማዊ፣ የቄሳር ዲናሮች፣ አጋፋሪ፣ አቦል ሚሊየነር፣ ስውር፣ ሳሎኑ፣ የብዕር ስም የተሰኙ ተጨማሪ የኪነ ጥበብ ስራዎችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡

በዲኤስቲቭ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ይዘቶችን በማዘጋጀት ላይ ያሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው ተቋሙ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ ከአፍሪካ አቻ የሙያ አጋሮቻቸው ጋር መፎካከር የሚያስችሉ ይዘቶችን እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

አፋፍ የተሰኘውን የአማርኛ ድራማ ለዲኤስቲቪ ተመልካቾች ለማድረስ እየሰራ ያለው አርቲስት ሚካኤል ሰለሞን በበኩሉ መልቲቾይዝ ኢትዮጵያ የሰጣቸው እድል የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብ በእጅጉ ያሳድገዋል ብሏል፡፡

በአቦል ቲቪ ሲተላለፉ የነበሩ እና እየተላለፉ ያሉ ፊልሞች ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊያን የምታገኘውን እና ኢትዮጵያም ለተቀረው አፍሪካዊያን የምታበረክታቸውን የኪነ ጥበብ ስራዎች እንደሚያሳድግም አርቲስት ሚካኤል አክሏል፡፡

ድርጅቱ ከአማርኛ ፕሮግራሞች በተጨማሪም በኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሚተላለፉ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ለተመልካቾች እንደሚያቀርብ ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡

የመልቲቾይዝ አፍሪካ ዳይሬክተር ፉሉፌሎ ባዱግላ በበኩላቸው “መልቲቾይዝ አፍሪካ አዳዲስ ይዘቶችን ለኢትዮጵያ እና ሌሎች አፍሪካዊያን በማቅረቡ ኩራት ይሰማዋል“ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መልቲቾይዝ ባ2022 ዓመት ብቻ በአፍሪካ በ40 ቋንቋዎች ከ6 ሺህ በላይ ሰዓት ይዘቶችን በ50 ሀገራት አቅርቧል የተባለ ሲሆን በየቀኑ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመልካች አለውም ተብሏል፡፡

መልቲቾይዝ ኩባንያ በአሁኑ ሰዓት 21 ሚሊዮን ሰብስክራይበር ያለው ሲሆን በአፍሪካ ቀዳሚ የመዝናኛ ፕሮግራምም ነው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *