“የኢትዮጵያ የረቂቅ ሙዚቃ እናት” እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ አረፉ


ፒያኖን በድንቅ ብቃት ስለሚጫወቱ “የፒያኖዋ እናት” የሚል ስያሜን ያገኙት እማሆይ ፅጌማርያም በ100 አመታቸው ነው ያረፉት
እማሆይ ጽጌማርያም ከ150 በላይ የረቂቅ ሙዚቃ ድርሰቶችን የጻፉ ሲሆን፥ ሦስት አልበሞችን በሲዲ እና በሸክላ ላይ ማሳተማቸውም ይታወሳል

በኢትዮጵያ ቀዳሚዋ የቫዮሊን እና ፒያኖ አቀናባሪ እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ በ100 ዓመታቸው አርፈዋል።
እማሆይ ፅጌማርያም ከአባታቸው ከአቶ ገብሩ ደስታ እና እናታቸው ወይዘሮ ካሣዬ የለምቱ በ1915 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ ነው የተወለዱት።

እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ በልጅነታቸው ለትምህርት በሄዱባት ስዊዘርላንድ ፒያኖን በደንብ ተምረዋል።

ከትምህርት መልስም በ19 አመታቸው ወደ ወሎ ግሸን ማርያም ገዳም በመሄድ በ21 አመታቸው ምንኩስናን መቀበላቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያሳያል።

ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም የውብዳር ሲሆን ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ መጠሪያቸው ወደ እማሆይ ፅጌማርያም ተቀይሯል።

እማሆይ ፅጌማርያም በድንቅ የፒያኖ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው ምክንያት “የፒያኖዋ እመቤት” የሚል ስያሜን ማግኘት ችለዋል።
ከ30 ዓመታት በፊት ደግሞ ወደ እስራኤል በመሄድ እየሩሳሌም ውስጥ በገዳማት ውስጥ ሲኖሩ ቆይተው በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ከ150 በላይ የረቂቅ ሙዚቃ ድርሰቶችን የጻፉ ሲሆን፥ ሶስት አልበሞችን በሲዲ እና በሸክላ ላይ አሳትመዋል።
አባታቸው ገብሩ ደስታ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን በአፄ ሃይለስላሴ ዘመንም የፓርላማ አፈ ጉባኤ በመሆን ማገልገላቸውን የቤተሰባቸው ታሪክ ያስረዳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *