የትግራይ አህጉረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትን እንዲያከብር ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ

የትግራይ አህጉረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትን እንዲያከብር ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ከሰሞኑ በትግራይ አህጉረ ስብከት በተሰጠ መግለጫ ዙሪያ ምላሽ ሰጥታለች።

ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ እንዳለችው በጦርነቱ ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት መካከል አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጻለች።

ይህንንም ተከትሎ በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም የባንክ ተቋማት ሥራቸውን በማቆማቸው በየጊዜው እንደሌሎች አህጉረ ስብከት ለትግራይ አህጉረ ስብከት ይላክ የነበረው በጀት መላክ አልተቻለም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ እርምጃ ምንድን ነው?


ቤተክርስቲያኗ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በቀኖናው መሰረት መፈታቱን ገለጸች
ምንም እንኳን በባንክ መዘጋት ለአገልጋይ ሠራተኞች በጀት መላክ ባይቻልም የደመወዝ መክፈያ የባንክ ሂሣባቸው በአዲስ አበባ ከፍተው ሲገለገሉ የቆዩት አባቶች በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በኋላ እስከአሁን ድረስ ያለምንም መቆራረጥ ወርኃዊ ደመወዛቸው ወደ ባንክ ሂሣባቸው ሲገባ ቆይቷል አሁንም እየገባ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ቋሚ ሲኖዶስ ፤ ቤተክርስቲያኗ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በጥናት ላይ በመመስረት ችግሩን ሊፈታ የሚችል የአቀራራቢ ሽማግሌ ልዑካንን ለመመደብ በዝግጅት ላይ እያለች መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኗን ጸንቶ የቆየ ተቋማዊ አንድነትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚንድ መልኩ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጽ/ቤት የሚል አዲስ ሕገወጥ ክልላዊ መዋቅር መፈጠሩን ከመግለጫው መሰማቱን የቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ያስረዳል።

ይህ ጽህፈት ቤት ጠርና ያለምንም በቂ ማስረጃ ዋናው መ/ቤት በጀት እንደከለከለ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ እንዳገደ፣ በአጠቃላይ በክልሉ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ላይ አቅዶ ችግር እንደፈጠረ የሚያስመስልና ሕገ-ቤተ ክርስቲያኑን የጣሰ መግለጫ ሠጥቷል ተብሏል።

ከመግለጫው በተጨማሪ በሕገ-ቤተ ክርስቲያኑ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በሁሉም አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡ የሚችሉት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ መሆኑ እየታወቀ ሆን ተብሎ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሥራ ላይ እያሉና ሲኖዶሳዊ አንድነቱ ጸንቶ ባለበት ሁኔታ ላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭና ያለቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራርን በጣሰ ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሊቃነ ጳጳሳት ተመድበው በሚሠሩባቸው የውጭ ዓለማት አህጉረ ስብከት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ከቀኖና ውጭ ራሳቸውን በራሳቸው በመመደብ መግለጫ መስጠታቸውን ቤተክርስቲያንን በእጅጉ እንዳሳሰዘነ ተገልጿል።

በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የባንክ አገልግሎት በመቆሙ የተከሰተ የግንኙነት መቋረጥ መሆኑን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኗ በጀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገር ለመላክ ዝግጁ መሆኗንም አስታውቃለች።

በክልሉ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የደረሰውን ጉዳትና ችግር ቅድስት ቤተ ክርስቲያኗ የተሰማትን ሐዘንና በችግሩም ወቅት ለአህጉረ ስብከቱ በበጀት ተደራሽ ባለመሆኗ ለተከሰተው ችግር ማዘኗን ገልጻለች።

ይህንንም የሚያስረዳ በቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ መግለጿን አስታውሳ የተከሰተው ጦርነት እንዲቆም በጸሎትና በምሕላ ስትማፀን መቆየቷ ወደጐን ተትቶና ተዘንግቶ የጦርነቱ ደጋፊ በሚያስመስል መልኩ የተሰጠውን መግለጫ ቤተ ክርስቲያኗ እንደማትቀበልም ገልጻለች።

በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ያለው አጠቃላይ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለመጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ መጠራቱም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግስትም በክልሉ የተከሰተውን የቤተ ክርስቲያኗን ተቋማዊ አንድነት እና ቀኖና የሚጥሰውን አደረጃጀት እንዲቆም ድጋፍ እንዲያደርግ ስትል ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *