ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከሰሞኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በአዲስ አበባ የነበሩት ጌታቸው ረዳ በትግራይ አዲስ የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መመረጣቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ (ቪኦኤ) የትግርኛው አገልግሎት ክፍል እንደዘገበው፣ ጌታቸው የማዕከላዊ ኮሚቴውን አብላጫ ድምጽ አግኝተዋል።

የቀድሞው የሕግ መምህር ጌታቸው ረዳ፣ በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የሕወሓት  ዋንኛ ተደራዳሪ የነበሩ ናቸው።

የሽግግር ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰች የምትገኘው ትግራይ ክልል፣ ከጦርነቱ አስቀድሞ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ስትመራ ነበር።

ከሰሞኑ በወጡ ዘገባዎች የፌዴራሉ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትግራይ በደብረጽዮን መሪነት እንድትቀጥል አይፈልጉም። ዋሺንግተን ፖስት ይዞት በወጣው ዘገባ ዐቢይ ለትግራዩ ጦርነት መጀመር ደብረጽዮንን ይወቅሳሉ።

የሕወሓት ሰዎች ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በይፋዊ መንገድ በጌድዮ ሃላላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲገናኙም ደብረጽዮን አልነበሩም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *