ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላን ለማሰብ ሮም ላይ በባዶ እግሩ ሊሮጥ መሆኑን አስታወቀ

የፊታችን እሁድ መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም የ2023 የሮም ማራቶን ይካሄዳል።

በዚህም ማራቶን ታሪክ ራሱን ይደግማል የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያዊው የባዶ እግር ሯጭ እንዲሁም ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ቁልፍ ዳይሬክተር በመሆን የሰራው የ45 ዓመቱ ኤርሚያስ አየለ ሙሉ ማራቶን በባዶ እግሩ ይሮጣል።

ኤርሚያስ አየለ ይህንን የሚያደርገው ለኢትዮጵያው ታላቅ አትሌት አበበ ቢቂላ ክብር እንዲሁም ለሀገር ገፅታ ግንባታ ሲል ነው።

” አበበ ቢቂላ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያው ጥቁር በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአፍራካውያን ስኬት መሰረት ጥሏል ” የሚለው ኤርሚያስ ” ሆኖም ግን ለሰራው ታሪክ የሚገባውን ያህል እውቅና እንዳላገኘ ይሰማኝ ነበር ” ብሏል።

ኤርሚያስ ፤ የአትሌት አበበ ቢቃላ ታሪክ ሁሌም እንደሚያነሳሳው ገልጾ ለዚህም እሱ ለአትሌቲክስ እና ለኢትዮጵያ ላደረገው ነገር ክብር እና ምስጋና ለመስጠት በተመሳሳይ ቦታ እና በተመሳሳይ መንገድ ታሪክ በሰራበት ቦታ በባዶ እግሩ እንደሚሮጥ አስረድቷል።

የሮም ውድድሩ  ቀላል እንደማይሆንና ስሜታዊም የሚያደርግ እንደሆነ የገለፀው ኤርሚያስ ” ይህን ትልቅ ትርጉም ያለውና ታሪካዊ ውድድር ለማድረግ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ” ብሏል።

ኤርሚያስ ውድድሩን ለመጨረስ እስከ አራት ሰዓት ሊወስድበት እንደሚች ገልጾ የሮሙ ማራቶን በመጪዎቹ 18 ወራት ከአበበ ቢቂላ ጋር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ግንኙነት ባላቸው በአቴንስ ፣ ቶኪዮ እና ፓሪስ ማራቶን በባዶ እግር ለሚያደርገው የማራቶን ሩጫ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግለት አመልክቷል።

የባዶ እግር የማራቶን ሩጫው አትሌት አበበ ቢቂላ ለሰራው ታሪክ ክብር ለመስጠት ከማድረግ ባለፈ ለሀገር ገፅታ ግንባታ ያለው አስታዋፆ ከፍተኛ ስለመሆኑ ገልጿል።

ኤርሚያስ ከዚህ ቀደም የታላቁ ሩጫን ሙሉውን ሁለት ጊዜ ፤ የሀዋሳ ግማሽ ማራቶን ሙሉ በባዶ እግሩ የሮጠ ሲሆን የሮም ማራቶን ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *