በሕገ ወጥ መንገድ የተሾሙ ጳጳሳት አህጉረ ስብከቶችን መልቀቃቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አገረ ስብከት በሦስት አባቶች ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ በሆነ መልኩ ለ25 አባቶች ሕገ ወጥ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት መሰጠቱ አይዘነጋም፡፡

ይህን ተከትሎም ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 በጠራው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባዔ፣ እነዚህን አካላት ከቤተክርስቲያን ሕብረት ለይቶ ማውገዙ፣ እንዲሁም በየትኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ እንዳይገኙ የእግድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

ችግሩ በእርቅ ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል በተደረገው ስምምነት መሰረት፣ በሹመቱ የተካተቱ አካላት ወደ ቀድሞ ሥማቸው እንዲመለሱ ስምምነት ከተደረገ በኋላም፤ ጉዳዩ በስምምነቱ መሰረት አለመፈጸሙን ቤተክርሰውቲያኗ በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡

ሕገ ወጥ የተባሉት ተሹዋሚዎች ከስምምነቱና ከሲኖዶስ ውሳኔ አፈንግጠው፣ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች በተለይም በወለጋ እና በምዕራብ አርሲ መንበረ ጵጵስናዎችን በኀይል ሰብረው ገብተዋል ተብሎ ነበር፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ ባለፈው ሳምንት ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት ላይ ምልዓተ ጉባዔ እስከሚያደርግበት ጊዜ ድረስ፣ እነዚህ አካላት በሕገ ወጥ መንገድ የያዙትን አቢያተ ክርስቲያናት ለቀው እንዲወጡ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡

በዚሁ መሠረት እነዚህ አካላት በሕገ ወጥ መንገድ የያዙዋቸውን አቢያተ ክርስቲያናት ለቀው መውጣታቸውን አዲስ ማለዳ ዘግባለች፡፡ 

በስምምነቱ መሰረት የተሾሙት አካላት ወደ ቀድሞ ቅስና ማዕረጋቸው ተመልሰው፣ ብቁ ሆነው የተገኙት ወደፊት በሲኖዶሱ ውሳኔ እንደሚሾሙና ብቁ ያልሆኑት በያዙት ማዕረግ እንዲገለግሉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ነገ ረቡዕ መጋቢት 6/2015 አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ እንደሚካሄድ ያስታወቀ ሲሆን፤ በዕለቱም በአዲስ አበባ አቅራቢያና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ አዳራሽ እንዲገኙ ጥሪውን ቀርቦም ነበር።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *