የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ አደገ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማደግ በኤሮስፔስ እና በተለያዩ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች በቅድመ ምረቃ እና ድሕረ ምረቃ ፕሮግራሞች ማስተማር ጀመረ።

የአቪዬሽን አካዳሚ የአቪዬሽን ስልጠና ፕሮግራሞችን በአብራሪነት፣ የአውሮፕላን ቴክኒሻን፣ የካቢን ሰራተኛ፣ የአየር መንገድ ሽያጭ እና አገልግሎት እና ሌሎች ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። 

ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካደገ በኋላ በኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ በቢኤስሲ ዲግሪ፣ በአውሮፕላን ጥገና ኢንጂነሪንግ በቢኤስሲ ዲግሪ፣ በአቪዬሽን ማኔጅመንት ቢኤስሲ ዲግሪ፣ በቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ቢኤ ዲግሪ እና ኤምቢኤ በአቪዬሽን ማኔጅመንት የመሳሰሉ የዲግሪ መርሃ ግብሮችን ጀምሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት “ከቀጣይ እድገትና ኢንቨስትመንት በኋላ 65 ዓመት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማደጉ በአየር መንገዳችን ረጅም እና ስኬታማ ጉዞ ውስጥ ሌላው ምዕራፍ ነው። እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን አመራር ይጠብቃል።” ብለዋል።

አክለውም፤ “ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ እና በድህረ ምረቃ የአቪዬሽን ፕሮግራሞችን በመስጠት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ቁርጠኛ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና ሌሎች አየር መንገዶችን በአካባቢው ያለውን የሰው ሃይል ፍላጎት የሚያሟሉ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን እና አመራሮችን ያፈራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የቀድሞው ኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የአሁኑ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም በበኩላቸው፤ ዩንቨርስቲው በፍጥነት እያደገ ላለው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍ እና በአጠቃላይ ለአህጉሪቱ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ይቀጥላል ብለዋል።

አካዳሚው ላለፉት 65 ዓመታት የፓይለት፣ የበረራ መስተንግዶ፣ የቴክኒሻንና የአገልግሎት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ15 ሺሕ በላይ የአቪዬሽን ሙያተኞችን በማሰልጠን ለአየር መንገዱ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ ባለፈው ወር በሐዋሳ ከተማ አዲስ የስልጠና ማዕከል መክፈቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ተመሳሳይ ማሰልጠኛዎችን በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በአሶሳና በሌሎች ክልሎች ለመክፈት እቅድ እንዳለዉም ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *