በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኩላሊት ህሙማን ቁጥር በርካቶችን ለችግር እየዳረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል ።
የህሙማኑን አቅም እየፈተነ የሚገኘው አቅምን ያላገናዘበ የህክምና ወጪ የብዙዎችን ቤት እያንኳኳ ይገኛል ሲሉ የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዳግማዊ ሚኒሊክ ፣ በዘውዲቱ እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች 180 ህሙማን የነፃ ህክምና አገልግሎት እየተጠቀሙ ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን ዕድሉን ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል።
እነዚህ ህሙማን ከእዚህ ቀደም በግል የህክምና ተቋማት ለአንድ ጊዜ የኩላሊት እጥበት ይጠየቁ ከነበረው ክፍያ እስከ 50 ከመቶ ጭማሪ እንደተደረገባቸው ስራ አስኪያጁ ያነሱ ሲሆን በግል የህክምና ተቋማት ለአንድ ጊዜ እጥበት ይጠይቅ የነበረው የ2000 ብር ክፍያ በአሁኑ ሰዓት ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ህሙማኑ 3000 ብር ለመክፈል መገደዳቸውን አንስተውልናል።
ይህንን መሰሉን የህሙማኑን ስቃይ የሚያቀል ስራ እየተከናወነ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በአማካይ ከ3 ሺህ የማያንሱ ዕድሮች ይገኝበታል ተብሎ የሚገመተውን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዕድሮችን ያሳተፈ ወርሀዊ መዋጮ እና ድጋፍ ማሰባሰብ ለማድረግ መታቀዱን ብስራት ሬድዮ ዘግቧል።
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ይህንኑ የዕድሮች ስብስብ በማንቀሳቀስ አቅሙን አጎልብቶ ለበርካታ ህሙማን ተደራሽ ድጋፍ ለመስጠት ማቀዱን አቶ ሰለሞን አሰፋ ጨምረው ተናግረዋል ።
ከእዚህ ቀደም ቋሚ ሰራተኞች ከወርሀዊ ደሞዛቸው ላይ የሁለት ብር ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት ያቀደው ድርጅቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ ሃላፊው ጠቁመዋል።