ለምግብ ማጣፈጫነት ከሚውሉ አትክልቶች መካከል ሽንኩርት አንዱ ነው። ሽንኩርት በዓለም ዙሪያ መሠረታዊ የምግብ ግብአቶች ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።
በበርካታ አገራት ሽንኩርት በድሃውም ሆነ በሃብታሙም ቤት የሚገኝ የምግብ አካል ሲሆን፣ ሥጋ ደግሞ እንደ ቅንጦት ምግብ የሚታይ ነው።
በፊሊፒንስ ግን ይህ በተቃራኒ ሆኗል፤ የሽንኩርት ዋጋ የትኛውንም አይነት ሥጋ ለመግዛት ከሚወጣው ገንዘብ በበርካታ እጥፍ ይበልጣል።
ለፊሊፒን ዜጎች ባለፉት ሳምንታት ጊዜ ሽንኩርት መሸመት ቅንጦት ሆኗል። ዋጋው በማሻቀቡ የተነሳ የሽንኩርት መግዣ ከሥጋ መግዣ በእጅጉ ንሯል።
በዚህ ሳምንት ፊሊፒንስ ውስጥ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 11 ዶላር (600 ብር ገደማ) ሲሆን፣ የአንድ ሙሉ ዶሮ ሥጋ ግን 4 ዶላር (220 ብር ገደማ) ብቻ ነው።
የሽንኩርት ዋጋ ንረት የፈጠረውን የገበያ ክፍተት ለመጠቀም ያለሙ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሽንኩርት ሲያስገቡ በአገሪቱ ባለሥልጣናት ተይዘዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ብቻ 310,000 ዶላር የሚያወጣ የሽንኩርት ጭነት፣ ልብስ ነው የሚል መለያ ተለጥፎበት ከቻይና በድብቅ ሲገባ ተይዟል።
በዋና ከተማዋ ማኒላ የሚገኙ ምግብ ቤቶች በሽንኩርት መጥፋት ምክንያት ሽንኩርት በርከት ብሎ የሚገባባቸው ምግቦችን ማቅረብ አቁመዋል። በተጨማሪም በርገር ላይ የሚጨመረው የሽንኩረት ለስሙ ጣል የሚደረግ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎችም በርገር ከምግብ ከዝርዝራቸው ወጥቷል።
ይህንን የሽንኩርት መጥፋት ለማካካስ አንዳንዶች ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው። ለዚህም ጣዕሙ የተለመደው አይነት ሽንኩርት ያልሆነ፣ መጠኑም በጣም ትንሽ የሆነውን በፊሊፒንስ ውስጥ የሚታወቅ የተለየ ሽንኩርት ዝርያ ለመጠቀም ተገደዋል።