ከዓመት ከስድስት ወር በኋላ የሚካሄደውን የፓሪስ ኦሊምፒክ እስከ 40 አገራት ያክል አድማ ሊመቱ እንደሚችሉ ፖላንድ አስጠነቀቀች።
የፖላንድ የስፖርት እና ቱሪዝም ሚኒስትር ካሚል ቦርትኒዙክ የፓሪስ ኦሊምፒክ ትርጉም አልባ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ይህ የሚስትሩ አስተያየት የተሰማው ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ የሩሲያ እና ቤላሩስ ዜጋ አትሌቶች እንዲሳተፉ ለመፍቀድ ማቀዱን ፖላንድ፣ ሊቱኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ላትቪያ በጋራ መቃወማቸውን ተከትሎ ነው።
ዩክሬን የሁለቱ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉ ከሆነ በውድድሩ አልገኝም ብላለች።
የኦሊምፒክ ኮሚቴው ግን በውድድሩ ላይ አድማ ማድረግ ትርፉ “አትሌቶችን መቅጣት ብቻ ነው” ብሏል።
የፖላንድ የስፖርት እና የቱሪዝም ሚንስትሩ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሳምንት በኋላ ከሚያደርገው ስብሰባ በፊት ግሬት ብሪቴን፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳን ጨምሮ 40 አገራት ውድድሩ ላይ አድማ እንዲመቱ ማሰባሰብ ይቻላል ብለዋል።
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች ገለልተኛ በሆነ ሰንደቅ ዓላማ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉበትን አማራጮች አጤናለሁ ብሎ ነው።
“የትኛውም አትሌት በፓስፖርቱ ምክንያት ከውድድር መታገድ የለበትም” ብሏል።
የዩክሬን የስፖርት ሚኒስትር ቫድያም ጉትሳኢት የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች ታግደው እንዲቆዩ የስፖርት አካላት ከዓለም ፌዴሬሽኖች ጋር ንግገራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።