አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

በኦሊምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በማውለብለብ ቀዳሚ የነበረው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ባደረበት ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የብስክሌት ስፖርተኛው ገረመው ደንቦባ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት በ90 ዓመቱ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ስትካፈል ከተሳተፉ ብስክሌተኞች ገረመው ደንቦባ አንዱ ነበር።

ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ በበርካታ የብስክሌት ውድድሮች ተሳትፎ ከ26 በላይ ዋንጫዎችን እና ከ32 በላይ ሜዳሊያዎችን ተሸልሟል።

አትሌቱ በስፖርቱ ዘርፍ ላበረከተው ጉልህ አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚያዘጋጀው የኢቢሲ ስፖርት አዋርድ 4ኛው የኢቢሲ-ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አትሌት ነበር።

ገረመው ደንቦባ ታኅሣሥ 7 ቀን 1925 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለደ።

እ.አ.አ በ1956 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በብስክሌት እና አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል።

በጎዳና ላይ በተደረገ የብስክሌት ግልቢያ ውድድር 24ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ያስመዘገበው ደረጃ ከአፍሪካ እና ከእስያ ተፎካካሪዎቹ ቀዳሚ አድርጎታል።

በውድድሩ ላይ ከገረመው በተጨማሪ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐይ ባሕታ እና መንግሥቱ ንጉሤ ተሳትፈዋል።

በጊዜው ኢትዮጵያ በብስክሌት በቡድን አራተኛ እንድትወጣ አስችለዋል።

17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በጣሊያን ሮም እ.ኤ.አ በ1960 ሲካሄድ ገረመው የተካፈለ ሲሆን የሌላ ሀገር ተወዳዳሪዎች በቴክኒካዊ ዘዴ የሚፈጥነውን ጎማ ጫፍ ከኋላ በመንካት ስለወረወሩት ትከሻው እና እግሩ ተሰብሮ በሔሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል መወሰዱ መረጃዎች ያሳያሉ።

የብስክሌት ቡድኑም በግልም ሆነ በቡድን ውጤት ሳያመጣ ቀረ።

ከጉዳቱ በኋላ ገረመው ወደ አሰልጣኝነት በመምጣት እ.ኤ.አ በ1968 ጃፓን ባዘጋጀችው 19ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካፈለውን ቡድን በአሠልጣኝነት አብሮ ተጉዟል።

እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው ሁለተኛ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌት ቡድን ይዞ በመጓዝ ወርቅ ይዞ ተመልሷል።

ገረመው ደንቦባ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ስኬታማ እንደሆነ ይነገርለታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *