ተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እርዳታ ጠባቂ ለሆኑ ኢትዮጵያውን ድጋፍ ለማድረግ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ።
ጽህፈት ቤቱ በአውሮፓውያኑ 2022 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯዊ አደጋዎች እና በግጭት ምክንያት አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል ብሏል።
ኦቻ ለዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ባወጣው ‘የኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ ዕቅድ’ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማቅረብ 3.99 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
አስቸኳይ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች መካከል 4.6 ሚሊዮን የሚሆኑት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መሆናቸው ተመላክቷል።
በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጋላጭ ከሆኑ ቀዳሚ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፣ በአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በቂ ዝናብ ባለመጣሉ ከፍተኛ ደርቅ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰቱን ድርጅቱ አስታውሷል።
‘የኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ ዕቅድ’ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተረጂዎች ቁጥር 13 ሚሊዮን እንደሚሆን ግምቱን አስቀምጧል።
ድርቁ በምሥራቅ እና በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ ላይ የምግብ ዋስትና እና እጥረት እንዲሁም የውሃ አቅርቦት ችግር ከማስከተሉም በላይ የበሽታ ወረርሽኝ የማስከተል አጋጣሚን ከፍ የሚያደርግ የጤና ስጋት መደቀኑ ተገልጿል።
ኦቻ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ግጭት ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ችግር ከመሆኑ ባሻገር ቀያቸውን ጥለው ለሚሰደዱ ሰዎች ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በተያዘው አውሮፓውያን ዓመት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ያተኩራሉ ብሏል።
እነዚህም አስቿይ ሕይወት አድን ሥራዎችን ማከናወን፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዲሁም ጉዳት የደረሰበት የማኅብረሰብ ክፍል ከጉዳቱ እንዲያገግም እና ችግሮችን መቋቋም እንዲችል ማስቻል ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነው ያለው ጽ/ቤቱ፤ ተፈጥሯዊ አደጋዎች እና ግጭቶች በአገሪቱ ካለው ደካማ ማኅበራዊ አገልግሎት ጋር ተደማምሮ ችግሩን አስከፊ እንዳደረገው አመልክቷል።