ባሏን የገደለችው ዝነኛዋ አትሌት ጉዳይ

አትሌት በሱ ሳዶ ከሁለት ወንድሞቿ እና ከሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በመሆን ባለቤቷን በመግደል ወንጀል ተከሳ ድርጊቱን መፈጸሟ በመረጋገጡ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባት።

በቅርበት የሚያውቋቸው የአዳማ አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ሐብታሙ ግርማ ስለ ግድያው ሲናገሩ “እኔ በጣም ነው ያዘንኩት፤ በእርሱ ሞትም በጣም አዝኛለሁ። የእርሷም እስር ከሞት የማይተናነስ በመሆኑ እና አገሪቱም እንዲህ ዓይነት ሰው በማጣቷ በጣም ነው ያዘንኩት” ብለዋል።

የአትሌት በሱ ሳዶ የቀድሞ አሰልጣኝ ስለ ሁኔታ ሲናገሩ የተፈጸመውን ወንጀል አምነው መቀበል እንዳዳገታቸው “እኔ አሁን ራሱ ይሄ ነገር እንዴት አንደተፈጠረ ሊገባኝ አልቻለም” ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል።

የመካከለኛ እና የረዥም ርቀት ሯጯ አትሌት በሱ ሳዶ እንዲሁም አብሯት የነበረው ወንድሟ ከባለቤቷ ግድያ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ እስራት በይኖባቸዋል።

ነገር ግን ሌላ ወንድሟ እና ከሻሸመኔ በገንዘብ ገዝቶ ያመጣቸው ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉ በተፈጸመበት ምሽት በማምለጣቸው እስካሁን በቁጥጥር ስር አልዋሉም።

አትሌት በሱ እና የቀድሞ አትሌት ከነበረው ባለቤቷ ተሻለ ታምሩ ጋር ከስምንት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ አብረው በትዳር መቆየታቸውን የፖሊስ ሰነድ ያስረዳል።

የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው ባለፈው ዓመት ነሐሴ 08/2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ ተሻለ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ተገድሏል።

የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ አየለ ኢማሙ፣ በዚያን ቀን በግምት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ የተፈፀመውን ነገር አስረድተዋል።

“ባል ተሻለ ውጪ ቆይቶ ሁለት ሰዓት አካባቢ ቤት ከገባ በኋላ፣ ሳሎን ተቀምጦ የእጅ ስልኩን በሚነካካበት ወቅት እነዚህ በገንዘብ የተገዙ ሰዎች ከተደበቁበት ወጥተው በብረት መትተው እና በስለት ወግተው ግድያውን ፈፀሙ።”

ከምርመራ በኋላ “እርሷም ከተባባሪዎቿ ጋር በመሆን ባሏን ያስገደለችው መሆኗን አምናለች” ሲል ዘገባው ያስረዳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *