በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ እና የውሃ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የተኮሱ የፀጥታ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ከቤት ያለመውጣት አድማ መምታታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከቤት ያለመውጣት አድማው ከተጀመረ ቀናት መቆጠራቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች የከተማዋ እንቅስቃሴም ሙሉ በሙሉ ተገድቧል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በከተማዋ ለወራት የተቋረጠው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ለመጠየቅ ባለፈው ሳምንት ጄሪካን ይዘው አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ 30 ሰዎች የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና ኢሰመኮ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በከተማዋ ትራንስፖርት፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመገበያያ መደብሮችም ሆነ የትኞቹም የመንግሥት ተቋማት ተዘግተው ከተማዋ ጭር ብላ መሰንበቷን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሰኞ ምሽት ገልጸዋል።
ሰልፈኞች ከተገደሉ በኋላ በተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ ሦስቱን ሰዎች ተኩሰው የገደሉ የፀጥታ ኃይል አባላት በሕግ እንዲጠየቁ፣ “ውሃ የጠማው ሕዝብ ውሃ እንዲሰጠው” ለመጠየቅም ሕዝቡ በራሱ ተሰባስቦ የጠራው አድማ ነው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠየቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል።
“ሕረተሰቡ በራሱ ፈቃድ ነው ቤት የተቀመጠው። አድማ የጠራ አካል የለም። የሕብረተሰቡ ጥያቄ አንድ እና አንድ ውሃ እና መሠረተ ልማቶች ይመለሱልን ነው” የሚል ነው ብለዋል ነዋሪው።
የውሃ አቅርቦት ችግር ለዓመታት የዘለቀ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪው በአሁኑ ወቅት ደግሞ “ሕዝቡ ውሃ መጠማቱን እየተናገረ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው ነዋሪም አድማ የጠራ፣ ወረቀት የበተነ አካል እንደሌለ ገልጸው፣ ውሃ ጠማን ያሉ ነዋሪዎች መገደላቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል ብለዋል።
ከሞቱት በተጨማሪ ከዚህ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የታሰሩ እና እስካሁን ያልተፈቱ ሰዎች እንዳሉ የገለጹት ነዋሪዎች መንግሥት ይህንን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም ብለዋል።
“የሞቱት ፍትህ ሊያገኙ ይገባል” በሚል ጥያቄያቸውን ከቤት ባለመውጣት እያሰሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ካለፈው ሳምንት አጋማሽ በኋላ በከተማዋ ፍተሻ እና እስሮች እንዳሉ ነዋሩዎች ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ በእስሩም የጉራጌ ክልልነት ጥያቄ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ሰዎች ኢላማ መሆናቸውንም ነው ነዋሪው የተናገሩት።
በከተማዋ ውስጥ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ እንደጀመር የፀጥታ ኃይሎች እና የአስተዳደር ባለሥልጣናት እየተዘዋወሩ ግፊት እያደረጉ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በወልቂጤ የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት የሥራ ማቆም አድማ ወደ አጎራባች አንዳንድ አካባቢዎች መዛመቱንም ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የክልሉም ሆነ የዞኑ መስተዳደር ነዋሪዎች አድማ እንዲመቱ ስላደረጋቸው ጥያቄ አስካሁን በይፋ የሰጡት ምላሽ የለም።