ለዓመታት በአፍሪካ ስፖርት ላይ ጥቁር ጥላውን እንዳጠላ ነው። በቅርቡ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የችግሩ ስፋት ታይቷል።
የስፖርተኞች የዕድሜ ጉዳይ።
ካሜሩን ባዘጋጀችው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ከነበሩት አገራት መካከል አንዷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነበረች። ነገር ግን ከጨዋታው ጅማሬ በፊት ከውድድሩ እንድትሰረዝ ተደርጓል።
ምክንያቱ ደግሞ ለውድድሩ ከተላኩት ተጫዋቾች መካከል 25ቱ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በላይ መሆናቸውን የኤምአርአይ ምርመራ በማሳየቱ ነው።
ከኮንጎ በተጨማሪ ቻድ እንዲሁ ተጫዋቾቿን ካሜሩን ከላከች በኋላ ከውድድሩ ተሰርዛለች።
የካሜሮን እግር ኳስ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ኤቶ የኤምአርአይ ምርመራ እንዲደረግ ካዘዘ በኋላ፣ ቻድ ለውድድሩ ካቀረበቻቸው ተጫዋቾች መካከል 30ዎቹ የዕድሜ ገደቡን አልፈዋል።
በመላው ዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖችን የሚያማክሩት የስፖርት ሳይንስ ባለሙያው በአፍሪካ ስፖርተኞች ላይ የሚታየው የዕድሜ ማጭበርበር መቆም እንዳለበት ቢስማሙም፤ ኤምአርአይ ግን የተጫዋቾችን ትክክለኛው ዕድሜ ለማወቅ ትክክለኛው አማራጭ ላይሆን ይችላል ይላሉ።
በሶለንት ዩኒቨርሲቲ ሳውዝሃምፕተን የስፖርት ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አደም ሆውኪ የኤምአርአይ ምርመራ የተጫዋቾችን ትክክለኛ ዕድሜ ማሳየት የሚችል አይደለም ይላሉ።
“በኤምአርአይ የሚደረግ ልኬት የአንድን ሰው ዕድሜ በትክክል ላያሳይ ይችላል” ይላሉ።
ቀድሞ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ በተከታታይ የኤምአርአይ ምርመራ ተደርጎ የእነዚህ ምርመራ ውጤቶች ካልተተነተኑ በቀር ስፖርተኛው ዕድሜው ስንት እንደሆነ ለማወቅ ያዳግታል ሲሉ ያስረዳሉ።
የተጫዋቾችን ዕድሜን ለመለካት ኤምአየርአይን መጠቀም በተመለከተ ስጋታቸውን የገለጹት ዶ/ር ሆውኪ ብቻ አይደሉም።
እአአ 2013 ላይ አሜሪካዊው አማካይ አቡቺ ኦቢንዋ የልደት ሰርተፊኬቱን ከተወለደባት አሜሪካ ቢያቀርብም የተደረገለትን የኤምአየርአይ የዕድሜ ምርመራ ማለፍ አልቻለም።
ይህ ተጫዋች ያቀረበው ሰነድ ተዓማኒ ከሆነ ምንጭ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ ምርመራው የተለየ ውጤት ማሳየቱ መነጋገሪ ሆኖ ነበር።