ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በቦረና በድርቅ ለተጎዱ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ለዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ለቦረና ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ የሚውል 1,000,000.00 (አንድ ሚልየን) ብር ለግሷል።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች በድርቅ መጎዳታቸው ሲታወስ ከ3 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳትም ሞተዋል፡፡

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ የዘንድሮን የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ በድርቅ ሳቢያ አስቸኳይ እርዳታ ለሚፈልገው የቦረና ሕዝባችን የ1ሚልየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በቦረና ዞን ለተከታታይ ለስድስተኛ ጊዜ ዝና ብ አለመዝነቡን ተከትሎ በድርቁ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የዞኑ አስተዳድር አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር 100 ሚሊዮን ብር በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ ሲያደርግ ሌሎችም የመንግስት እና የግል ተቋማትም ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከ28 ሚሊዮን በላይ እንደደረሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለው ግጭት እንዲሁም ድርቅ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ቁጥር አሻቅቦታል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ኬንያ ለመላክ በሂደት ላይ ስትሆን በርካቶች ግን በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ ሆነው ለምን ስንዴው ወደ ውጪ ሀገራት ይላካል የሚሉ ጥያቄዎችን እና ትችቶችን በመንግስት ላይ በማንሳት ላይ ናቸው፡፡
የዱቄት ፋብሪካዎች እና ምግብ ማቀነባበሪያዎች በበኩላቸው በስንዴ እጥረት ምክንያት የምርት እጥረት እንዳጋጠማቸው አስታውቀዋል፡፡

መንግስት በበኩሉ የስንዴ እጥረት አንዲከሰት እያደረጉ ያሉት ፋብሪካዎች ናቸው በሚል በአንድ ኩንታል ስንዴ ምርት ላይ የ4 ሺህ ብር ዋጋ ተመን አውጥቷል፡፡

አርሶ አደሮች ግን የመንግስትን የዋጋ ተመን በመቃወም ስንዴያቸውን በተቀመጠላቸው ዋጋ ላለመሸጥ በመቃወም ላይ ይገኛሉ፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *