የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ከተማዎች እንደ አዲስ እንዲደራጁ ውሳኔ አሳለፈ


የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 3ኛ መደበኛ 6ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ ዓመት ስብሰባ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ከተማዎች እንደ አዲስ እንዲደራጁ ውሳኔ አሳልፏል።

የአሮሚያ ክልል መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ኑሮ እና ተጠቃሚነት በመሠረታዊነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ፈጣን፣ ዘላቂ እና ሰፊ መሠረት ያለው ልማት በማስመዝገብ የተለያዩ የልማት ስትራጂዎችን በማመንጨት ስትራቴጂዎቹን ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችንና አሠራሮችን በመዘርጋት ሲሠራ መቆየቱን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውሷል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የከተማ ልማት ለማካሄድ በከተመዎቹ የዕድገት ደረጃ መሠረት በርካታ ከተሞችን በመመሥረት ሰፋፊ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም አሁን በተደረበት የዕድገት ደረጃ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ በመሆን ሕዝቡን እና ክልሉን የሚመጥኑ ከተሞችን ለመፍጠር እንዲሁም ሕገ-ወጥነትን በመቆጣጠር በከተሞች ውስጥ እየታዩ ያሉ ውስብስብ ሁኔታዎችን ለማስተዳደር ያለውን አደረጃጀት እየፈተሹ እና እያሻሻሉ መሄድ አስፈላጊ ነው ብሏል የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ።

በመሆኑም ከተሞቹ ያላቸውን መልካም ዕድል ወደ አንድ በማምጣት አብረው እንዲለሙ እና የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸው፣ በአንድ ፕላን በመተዳር ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲኖራቸው፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ኖሯቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ሙያን ለማስፋፋት፣ የቢዝነስ አስተሳሰብን ለማዳበር እና የአገልግሎትን ለማሻሻል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁለት እና ከዚያ በላይ ከተሞችን አንድ ላይ ለማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ የከተሞቹ አደረጃጀት እንደሚከተለው ተከናውኗል።

  1. ቢሾፍ ከተማ፦ የቢሾፍቱ ከተማ፣ ዱከም ከተማ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት ከተሞች ሂዲ፣ ኡዴ ደንካካ እና ዲሬ በመቀላቀል በ3 ክፍለ ከተሞች እና በ10 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
  2. ሻሸመኔ ከተማ፦ የሻሸመኔ ከተማ እና የቢሻን ጉራቻ ከተማ በመቀላቀል በ4 ክፍለ ከተሞች እና በ12 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
  3. አዳማ ከተማ፦ የአዳማ ከተማ እና የወንጂ ከተማን በመቀላቀል በ6 ክፍለ ከተሞች እና በ19 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
  4. ሮቤ ከተማ፦ የሮቤ ከተማ እና የጎባ ከተማን በመቀላቀል በ3 ክፍለ ከተሞች እና በ12 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
  5. ማያ ከተማ፦ የሀረማያ ከተማ፣ የአወዳይ ከተማ እና የአዴሌ ከተማን በመቀላቀል በ3 ክፍለ ከተሞች እና በ12 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
  6. ባቱ ከተማ፦ የባቱ ከተማ እና የአዳሚ ቱሉ ከተማን በመቀላቀል በ7 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመልማት ዕድል ያላቸው ከተሞቻን በተሟላ መንገድ በመጠቀም ሁለንተናዊ የሆነ ልማት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉትን ከተሞች እና ወረዳዎችን ልማት እንዲያፋጥኑ ለማድረግ እና የአመራርን ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚከተሉት ከተሞች ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግሥት እንዲሆን ተወስኗል።

  1. መቱ ከተማ
  2. አጋሮ ከተማ
  3. ቡሌ ሆራ ከተማ
  4. ነጆ ከተማ
  5. ሰንዳፋ በኬ ከተማ
  6. ሸኖ ከተማ
  7. ሞያሌ ከተማ
  8. ዶዶላ ከተማ
  9. ሻኪሶ ከተማ

በተመሳሳይ መልኩ የከተሞች የማስፈፀም አቅማቸው ተሻሽለው ፈጣን እና ከእንግልት የፀዳ አገልግሎት በሙሉ አቅም እንዲሰጥ እና ሁሉአቀፍ የሆነ ልማት እንዲመዘገብ ለማድረግ እንደ አጠቃላይ እየተደረገ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የከተሞችን ዕድገት መሠረት በማድረግ የከተሞችን ደረጃ እንደሚከተለው እንዲሻሻል ተወስኗል።

  1. አዳማ፣ ሻሻመኔ እና ቢሾፍቱ ከተሞች፡- የሬጂዮ-ፖሊስ ከተማ
  2. የሮቤ ከተማ እና የማያ ከተማ፡- ዋና ከተማ
  3. የመቱ፣ አጋሮ፣ ቡሌ ሆራ፣ ነጆ፣ ሰንዳፋ በኬ፣ ሞያሌ እና ሻኪሶ ከተሞች፣- ወደ ከፍተኛ ከተማነት እንዲያድጉ ተወስኗል።

በሌላ መልኩ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የቆየውን የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ለማስመዝገብ፣ በድንበር አካባቢ ያለውን ሕገ ወጥነትን ለመቅረፍ፣ በድንበር አካባቢ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚከሰተውን የሰላም ሁኔታን ለመፍታት እንዲሁም ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ ውጤታማ የሆነ አደረጃጃት እና አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የምሥራቅ ቦረና ዞን አዲስ ዞን ሆኖ እንዲደራጅ ተወስኗል።

በአዲስ መልክ 21ኛ ዞን ሆኖ የተደራጀው የምሥራቅ ቦረና ዞን ዋና ከተማው ነጌሌ ቦረና ሆኖ፡-

• ከቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ፣ ሞያሌ ከተማ፣ ጉቺ ወረዳ እና ዋችሌ ወረዳ፣
• ከጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ፣ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳ፣ ነጌሌ ቦረና ከተማ፣
• እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ ወረዳ፣ ኦቦርሶ ወረዳ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳ በመጨመር እንደ ዞን 10 ወረዳዎችን በመያዝ እንዲደራጅ ተደርጓል።

በአዲሱ አደረጃጀት የምሥራቅ ቦረና ዞን በአዲስ መልክ የተደራጀ ሲሆን የጉጂ ዞን ዋና ከተማ አዶላ ሬዴ ሆኖ የቦረና ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ያቤሎ ከተማ እንዲሆን ተወስኗል።

በልላ በኩል ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሆነ አደረጃጀት ለመፍጠር የመሬት ስፋት፣ የፀጥታ ችግር፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እና ፈጣን ልማት ጥያቄን ለማረጋገጥ የመደ ወላቡ ወረዳ የነበረ በሁለት ቦታ ማለትም የመደ ወላቡ ወረዳ እና ኦቦርሶ ወረዳ ሆኖ እንዲደራጅ እና የጭናክሰን ወረዳ የነበረ በሁለት ወረዳ ማለትም የጭናክሰን ወረዳ እና የመከኒሳ ኦሮሞ ወረዳ ሆኖ እንዲደራጅ መወሰኑን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *