በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተቋቋመዉ በሸገር ከተማ አስተዳደር ሱሉልታ ከተማ ልዩ ስሙ ቀርዮ የተሰኘዉ ነዋሪዎች ቤታቸዉ እየፈረሰባቸዉ እንደሆነ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤታቸዉ ድንገት ስለሚፈርስባቸዉ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸዉን ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡
ቤቶቹ ያለምን ማስጠንቀቂያ ድንገት በሌሊት ጭምር እየፈረሱ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ “እቃችንን እንኳን ለማንሳት ጊዜ አልተሰጠንም” ብለዋል፡፡
ቤቶቹን ማፍረስ ብቻም ሳይሆን የቤት ክዳን ቆርቆሮና በር ጨምር እየተወሰደበናቸዉ እንደሆነም ሰምተናል፡፡
አሁን ላይ ቤት የፈረሰባቸዉ ዜጎች ጊዚያዊ ማረፊያ አጥተዉ ሜዳ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ነዋሪዎቹ ፤ ግማሾቹም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰደዱ ነዉ ተብሏል፡፡
“ቤቶቹ ህገወጥ ሆነዉ ቢገኙ እንኳን እንድናፈረስና ለቀን እንድንወጣ ጊዜ መሰጠጥ ነበረበት” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግስት ይድረስልን ሲሉ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን አዲስ የተመሰረተዉን የሸገር ከተማ አስተዳደር ለማናገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም፡፡
በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩም ሆነ የሚመለከተዉ አካል ምላሸ የሚሰጥ ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡